ቀለማትና ትርጉማቸው
በኑሯችን ውስጥ የምናያቸው ቀለማት የራሳቸው የሆነ ትርጉም አላቸው። ቀለማት በውስጣችን ለሚሠማን ስሜትም እጅግ ትልቅ ሚና አላቸው። ይህን ፅሁፍ በምታነቡበት ግዜ ያላችሁበት ክፍል(ቦታ) ምን አይነት ቀለም አለው? የለበሳችሁት ልብስስ ምን አይነት ቀለም ነው? ምን አይነት ስሜት እያሳደረባችሁ እንደሆነ ለማጤን ሞክሩ። አንድን ቁሳቁስ(ክፍል) ቀለም በምንሠጠው ግዜ በሰዎች ላይ መፍጠር የፈለግነውን ስሜትም መርጠናል ማለት ነው። ለምሳሌ በሰንደቅ አለማችን ላይ ያሉት ቀለማት አረንጓዴ –የኢትዮጽያን ልምላሜ፣ ቢጫ– የሀገሪቱን ተስፋ እናም ቀይ–የሀገር ፍቅርንና መስዋዕትነትን በመግለፅ በእኛ ላይ የኢትዮጽያዊነትን ስሜት የመፍጠር አቅም አላችው ።
ቀይ
ቀይ ከፍተኛ የሆነ ሞገድ ያለው በመሆኑ ከሌሎች ቀለማት ጎልቶ የመታየት አቅም ያለው ኃይለኛ የሆነ ቀለም ነው። እሳት፣ ሙቀትና ቁጣን ሊገልፅልን የሚችለው ቀይ ቀለም በራስ የመተማመን ስሜታችንን ይጨምራል። በቢሮዎች እና የፈጠራ ስራ በሚሠራባቸው ቦታዎች መጠቀም ሠራተኞችን ቆራጥና ቀልጣፋ ለማድረግ ይረዳል። የቢሮዎችን ኮለም ወይም የእንግዳ መቀበያ ዴስክ ጀርባ ያለ ግድግዳን ቀይ ቀለም ብንቀባው ደማቅ መግቢያ ይሆናል፡፡በቤታችን ውስጥም በሳሎንና በማብሰያ ቦታ አልፎ አልፎ በመጠቀም ለቦታው ድምቀት መስጠት እንችላለን።ቢጫ
ቢጫ ከተስፋ ፣ ደስታ እና መነቃቃት ጋር የሚያያዝ የቀለም አይነት ነው። ቢጫ ከፀሐይ ጋር የሚገናኝ ቀለም በመሆኑ በቤት ውስጥ ዲዛይን ስንጠቀመውም ክፍሉን ሞቃታማ ስሜት የመስጠት አቅም አለው። ቢጫ ቀለም በጥናት ወቅት መነቃቃትን ከመጨመር በተጨማሪ ውሳኔዎችን ለመወሰን ይረዳናል፡ ለወጥ ቤት ለመታጠቢያ ቤት ለኮሪደርና ለጠባብ ቤት ዋና መግቢያ ተመራጭ የሆነ ቀለም ነው፡፡፡ ቢጫ በፍጥነት ስሜትን የመያዝ አቅም ቢኖረውም ያለአግባብ በምንጠቀምበት ግዜ ግን ዓይንን የማድከም ጠባይ አለው።
ሰማያዊ
የሰማይ እና የውቅያኖስ (ባህር) ቀለም የሆነው ሰማያዊ ከፍተኛ የሆነ የማረጋጋትና የማቀዝቀዝ አቅም አለው። በየትኛውም የክፍል አይነት መጠቀም ብንችልም በመኝታ ቤትና በመታጠብያ ቤት ብንጠቀመው አብዛኛውን ግዜ ይመከራል።
ብርቱካናማ
አረንጓዴ
የቢጫና የሰማያዊ ቅይጥ የሆነው አረንጓዴ ተፈጥሮን የሚገልፅ ቀለም ነው። የሁለቱ ቀለማት ቅይጥ እንደመሆኑም በሰማያዊ ቀለም የምናገኘውን የመረጋጋት ስሜትና በቢጫ ውስጥ ያለውን የሙቀትና የደስታ ስሜት አጣምሮ የያዘ የቀለም አይነት ነው። ስለዚህም በየትኛውም የክፍል አይነት ልንጠቀመው እንችላለን። አረንጓዴን እንዴት በቤት ውስጥ መጠቀም እንዳለብን ተፈጥሮ ትልቅ አስተማሪ ነው። ለምሳሌ በሜዳ ላይ ያለን ሳር ተመልከቱ በየቦታው ጣል ጣል ያሉ የተለያዩ ቀለም ያላቸው አበባዎች እንዴት እንደሚያሳምሩት። ስለዚህም ከአረንጓዴ ጋር የሚሄዱ የተለያዩ ቀለማትን በመጠቀም ውበቱን መጨመር እንችላለን።
እነዚህን በሀገራችን ውስጥ የሚዘወተሩትን ቀለማት እንደ ምሳሌ ያህል በጥቂቱ አነሳን እንጂ ወደ አስር ሚሊዮን የሚጠጉ የቀለም አይነቶችን ዓይናችን መለየት ይችላል። በቀጣይም እንዴት ዋና የሚባሉትን ቀለማት ( ቀይ፣ ቢጫ፣ ሰማያዊ ) እየቀየጥን እንዴት ልዩ ልዩ ቀለማትን መፍጠር እንደምንችል እንመለከታለን። እስከዛው ድረስ እናንተ የምትወዱትን ቀለምና ለምን እንደምትወዱት ከፎቶ ጋር ብትልኩልኝ ደስ ይለኛል። ጥያቄዎቻችሁንም ለመመለስ ዝግጁ ነኝ። በነገራችን ላይ እዚህ ጽሁፍ ላይ ለምሳሌ የተጠቅምኩባቸውን ስዕሎች ያገነኘኋቸው ከinternet ላይ ነው።
salome@baroqueinethiopia.com

Comments
Post a Comment