ኪነ-ህይወት በዘበናይ ዘይቤ
LIFESTYLE
ዘይቤ & ባህል
ኪነ-ህይወት በዘበናይ ዘይቤ፦ ከቁስ ክምችት ወደ እውነተኛ ብልጽግና
በዚህ ጽሑፍ ውስጥ፣ የዘመናዊ ኑሮ ጥበብን እና የዋቢ-ሳቢ ፍልስፍናን እንመረምራለን። ቀላልነት፣ ተፈጥሯዊ ውበት፣ እና ሆን ተብሎ የተመረጠ ዲዛይን እንዴት ህይወታችንን እንደሚለውጥ እንመለከታለን።
ቀላልነት የመጨረሻው ውስብስብነት ነው።
እንደምታውቁት እኔ የጃፓናውያንን "ኢኪጋይ" (Ikigai)
የህይወት ፍልስፍና በጥልቀት እወደዋለሁ። በቅርቡ ደግሞ ከዚህ ፍልስፍና ጋር የሚቀናጅ፣ እለት ተእለት አኗኗራችንን እና ከቁስ ወይም
ከገንዘብ ጋር ያለንን ግንኙነት ይበልጥ የተቃኘ እና ትርጉም ያለው የሚያደርግ አንድ ድንቅ ፅሁፍ አግኝቼ፤ ለእናንተ ለውድ የዘበናይ
እህቶቼ ላካፍላችሁ ወደድኩ።
ፅሁፉ ወጪያችንን በጥበብ እየቀነስን፣ ውስጣዊ ሰላማችንን እና የህይወት ጥራታችንን
በከፍተኛ ሁኔታ የምናሳድግበትን ስምንት ድንቅ የጃፓን መርሆች በጥልቀት ይዳስሳል። መልካም ንባብ ይሁንልን!
የበለጠ ባለጸጋ የመሆን ሚስጥር ብዙ ገንዘብ ማግኘት ሳይሆን ፍላጎታችንን መቀነስ ቢሆንስ?
አለማችን ገንዘብ በማውጣት፣ በአዳዲስ ነገሮች እና ቀጣዩን ትልቅ ስኬት በማሳደድ በተጠመደችበት በዚህ ዘመን፤ በትንሽ ነገር የመኖርን ጥበብ የተማረ አንድ ባህል አለ። ይህ የመቸገር ወይም ራስን የመቅጣት ጉዳይ ሳይሆን፥ በማሰብ እና በማስተዋል የመኖር ጥበብ ነው።
ጃፓን ሰዎችን ገንዘብ እንዴት መቆጠብ እንዳለባቸው ብቻ አይደለም የምታስተምረው፤ ይልቁንም አነስተኛ ወጪ እያወጣን እንዴት የተሻለ ህይወት መኖር እንደምንችልም ነው። አንዴ እነዚህን መርሆች ከተረዳን፣ ለገንዘብም ሆነ ለህይወት ያለን እይታ ዳግመኛ እንደበፊቱ ላይሆን ይችላል።
በዘመናዊው ማህበረሰባችን ውስጥ፣ ሁልጊዜም "ብዙ" ነገር፣ ብዙ ገቢ፣ ብዙ ንብረት፣ ብዙ ምቾት፣ ብዙ ቅንጦት ሲኖረን ኑሮአችን የተሻለ እንደሆነ እንዲመስለን ያረገናል።
ነገር ግን ይህ ሁሉ "ብዙ" ነገር እያለን እንኳ፥ ሁላችንም የመጨናነቅ፣ የገንዘብ እጥረት እና የስነ-አእምሮ ድካም ይሰማናል። አሁን እስኪ የተለየ አካሄድን እናስብ፤ ወጪዎቻችን በተፈጥሮአዊ መንገድ የሚቀንሱበትን፣
ውጥረታችን የሚቀንስበት እና ደስታችን በዝምታ የሚያድግበት ህይወት። ይህ ህልም አይደለም፤ በጃፓን ባህል ውስጥ በጥልቀት የተተከለ ፍልስፍና ነው። ከቀላል (ሚኒማሊስት) ቤቶች ጀምሮ እስከ ማስተዋል የተሞላበት የወጪ ልማዶች ድረስ፥ ጃፓኖች ቀለል ያለ ኑሮን፣
ስነ-ስርዓትን እና እርካታን የሚያመጣጥኑ በጊዜ የተፈተኑ የኑሮ ዘይቤዎችን አዳብረዋል።
በዚህ ፅሁፍ አነስተኛ
ወጪ አውጥተን በተሻለ ሁኔታ ለመኖር የሚያስችሉንን ስምንት ጠንካራ የጃፓን መንገዶችን እንመረምራለን፤ እነዚህ ልማዶች ገንዘብን ለመቆጠብ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ የህይወት ተሞክሯችንን የሚቀይሩ ናቸው።
1. ካኬቦ (Kakeibo)፦ የሰከነ የገንዘብ አወጣጥ ዘዴ 📓 ✍️
ይህ የመጀመሪያው መርህ እጅግ በጣም ቀላል ግን በሚያስደንቅ ሁኔታ ጠንካራ የሆነ ነገር ነው። "ካኬቦ" ይባላል። ካኬቦ ባህላዊ የጃፓን የበጀት አያያዝ ዘዴ ነው፤ ነገር ግን ስለ ቁጥሮች ብቻ አይደለም። ስለ የገንዘብ አጠቃቀም ግንዛቤ
ነው። በደፈናው ወጪዎቻችንን ከመከታተል ወይም በስልክ መተግበሪያዎች ላይ ከመደገፍ ይልቅ፥ ካኬቦ በብዕር እና በወረቀት ተቀምጠን እንድናስብ ያደርገናል። በየወሩ ራሳችንን አራት ቁልፍ ጥያቄዎችን እንጠይቃለን፦
- ምን ያህል
ገንዘብ አለኝ?
- ምን ያህል
መቆጠብ እፈልጋለሁ?
- በትክክል ምን ያህል
እያወጣሁ ነው?
- እንዴትስ ማሻሻል እችላለሁ?
ነገር ግን ነገሩን ወደ ትልቅ ለውጥ የሚቀይረው እዚህ ጋ ነው፤ እያንዳንዱ
ወጪያችን በአራት ቡድኖች ይከፈላል፦
1)
አስፈላጊ ነገሮች (Needs)፣
2)
ምኞቶች/ፍላጎቶች (Wants)፣
3)
መዝናኛ(entertainment) እና
4)
ያልታሰቡ ወጪዎች (Unexpected)።
ይህ በፀፀት ሳይሆን በታማኝነት ልማዶቻችንን እንድንጋፈጥ ያስገድደናል። የባህሪያችንን አዝማሚያ ማየት እንጀምራለን። ያለምክንያት በድንገት የምንገዛቸው ነገሮች በግልጽ ይታዩናል። አላስፈላጊ ወጪዎቻችን ልንክደው በማንችለው ሁኔታ
ጎልተው ይወጣሉ፤ ቀስ በቀስም አንድ ነገር ይቀየራል። በዘፈቀደ ማውጣትን አቁመን አስበንበት ማውጣት እንጀምራለን። ውጤቱም፦ አነስተኛ ብክነት፣ ከፍተኛ ቁጠባ እና ከገንዘብ ጋር ያለን ግንኙነት ጥልቅ መረዳት ይሆናል።
2. ዳንሻሪ (Danshari)፦ ቤታችንን ብቻ ሳይሆን ህይወታችንን እናፅዳ፣ 🍃 🧹
በጃፓን "ሚኒማሊዝም" (በጥቂት ነገር መኖር) ውበት ብቻ አይደለም፤ የማሰብ መንገድም ጭምር ነው። ይህ ፍልስፍና "ዳንሻሪ" በመባል ይታወቃል። በደፈናው ሲተረጎም፦ የማይፈልጉትን ነገር አለመቀበል፣ የማይጠቀሙበትን ማስወገድ እና ከእንግዲህ ለማያገለግሉን ነገሮች አለመጨነቅ (መለየት) ማለት ነው። በዋናነት ዳንሻሪ ስለ ነፃነት ነው። እስኪ እናስብበት፤ የእኛ የሆነ እያንዳንዱ ቁስ ቦታ ይይዛል። አካላዊ ቦታ ብቻ ሳይሆን አእምሯዊ ቦታም ጭምር። ብዙ ባለን ቁጥር፣ የምናስተዳድረው ነገር ይበዛል። ብዙ ባስተዳደርን ቁጥር ደግሞ የምናወጣው ጉልበት ይጨምራል። የእኛ የሆኑትን ነገሮች በመቀነስ፣ እኛን የሚቆጣጠሩንን ነገሮች እንቀንሳለን። የገንዘብ ጥቅሙም ይሄው ነው፦ የማይፈልጉትን ነገር መግዛት ስናቆም፣ ወጪያችን በተፈጥሮው ይቀንሳል። ነገር ግን ትልቁ ስጦታ የአእምሮ ጥራት (ግልጽነት) ነው፤ የጸዳ ቦታ ወደ ረጋ አእምሮ ይመራል፣ የረጋ አእምሮ ወደተሻለ ውሳኔ ይመራል፣ የተሻለ ውሳኔ ደግሞ ወደ ተሻለ ህይወት ይመራናል።
3. ሞታይናይ (Mottainai)፦ አሁን ላለን ነገር ክብር እንስጥ ♻️ 🤲
ጥልቅ ስሜታዊ ክብደት ያለው አንድ የጃፓን ቃል አለ፤ "ሞታይናይ" ይባላል። በብክነት ላይ የሚሰማንን የቆጨታ ስሜት ይገልጻል። የገንዘብ ብክነትን ብቻ ሳይሆን የጊዜን፣ የሀብትን እና የእቅማችንን ብክነት ጭምር። በጃፓን አንድን ነገር መጣል በቀላሉ የሚታይ ነገር አይደለም። ሰዎች ላላቸው ነገር ክብር እንዲሰጡ ይማራሉ። ልብሶቻቸውን ይሰፋሉ (ያድሳሉ) እንጂ አይቀየሩም። ምግባቸው ሙሉ
በሙሉ ጥቅም ላይ ይውላል እንጂ አይባክንም። እቃዎቻቸውን
ይንከባከባሉ እንጂ አይጥሉም። ይህ የአስተሳሰብ ለውጥ ሁሉንም ነገር ይቀይረዋል። ሁልጊዜ አዳዲስ ነገሮችን ከመፈለግ ይልቅ፣ እጃችን ላይ ያሉንን ነገሮች ማድንቅ እንጀምራለን። አድናቆታችን ሲያድግ ደግሞ ፍጆታችን (ግዢያችን) በተፈጥሮው ይቀንሳል። ሞታይናይ የሚያስተምረን እውነተኛ ብልጽግና የሚገኘው ማለቂያ በሌለው ቁሳቁስ ክምችት ውስጥ ሳይሆን፣ ባለን ነገር ትርጉም ባለው መልኩ መጠቀም ላይ መሆኑን ነው።
4. ዋቢ-ሳቢ (Wabi-Sabi)፦ ፍፁም ባልሆነ ነገር ውስጥ ውበትን ማግኘት 🏺 ✨
የዘመኑ የሸማች ባህል የሚኖረው በ"ፍፁምነት" ላይ ነው። እንከን የለሽ ምርቶች፣ አዳዲስ ዲዛይኖች፣ በየአመቱ የሚደረጉ ማሻሻያዎች የዘመኑ የሸማች ባህል ነው። ነገር ግን የጃፓን ፍልስፍና የተለየ እይታን ያቀርብልናል፤ "ዋቢ-ሳቢ" ይባላል። ከኢኪጋይ ቀጥሎ ሌላው በጣም የምወድው የጃታን ፍልስፍና ነው። ዋቢ-ሳቢ ማለት ፍፁም ባልሆኑ፣ ቀላል በሆኑ እና ባረጁ ነገሮች ውስጥ ውበትን የማግኘት ጥበብ ነው። በወርቅ የተጠገነ የተሰነጠቀ ሳህን፣ የቆየ የእንጨት ጠረጴዛ፣ የደበዘዘ የጨርቅ ቁራጭ፤ እነዚህ እንደ ጉድለት ሳይሆን እንደ ታሪክ ነው የሚታዩት። ዋቢ-ሳቢን ስንቀበል አንድ ትልቅ ነገር ይከሰታል፤ ፍፁምነትን ማሳደድ እናቆማለን። ነገሮችን አዲስ ስላልሆኑ ብቻ መቀየር እናቆማለን። ከነገሩ አዲስነት ይልቅ ለባህሪው (ለታሪኩ) ዋጋ መስጠት እንጀምራለን። ይህ ሽግግር ደግሞ በዝምታ ገንዘባችንን ይቆጥብልናል፤ ምክንያቱም ሁልጊዜ አዲስ ነገር የመግዛት አዙሪት ውስጥ አንጠመድም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሰላምን ያመጣልናል፤ ምክንያቱም ህይወት ራሷ ፍፁም አይደለችም፣ ያንን መቀበል መማር ደግሞ ትልቁ የነፃነት መንገዳችን ነው።
5. ኢኪጋይ (Ikigai)፦ ከቁሳቁስ ይልቅ አላማ ይቅደም 🎯 🌱
ከጃፓን እጅግ ጠንካራ ፍልስፍናዎች አንዱ በጣም ግላዊ የሆነ ነገር ነው፤ "ኢኪጋይ" ይባላል። ጠዋት ከእንቅልፋችን የምንነቃበት ምክንያት፤ ጉዟችንን ለመቀጠል ያለን የዝምታ ተነሳሽነት ማለት ነው።
ነገር ግን ኢኪጋይ በአንድ ጀምበር ድንገት የምናገኘው ነገር አይደለም፤ በህይወታችን ውስጥ እንደተደበቀ ክር ቀስ በቀስ፣እየተመዘዘ የምናገኘው
ነገር ነው። በዋናነት ኢኪጋይ የሚኖረው በአራት ቀላል ግን ጥልቅ ጥያቄዎች መገናኛ ላይ ነው፦
- ምን እንወዳለን?
- በተፈጥሯችን በምን ነገር ላይ ጎበዝ
ነን?
- አለም ከእኛ ምን ትፈልጋለች?
- በተጨባጭ በምን ነገር ልንካስ (ሊከፈለን) ይችላል?
እነዚህ አራቱ የሚገናኙበት ቦታ፥ አላማችን የሚጀምርበት ነው። ነገር ግን ማለቂያ በሌለው ወጪ አለም ውስጥ ይህንን ፍልስፍና ጠንካራ የሚያደርገው ምንድን ነው? አብዛኞቻችን ባንረዳውም፥ አብዛኛው ዘመናዊ የፍጆታ ግዢያችን ስሜታዊ ነው። ነገሮችን ሁልጊዜ ስለሚያስፈልጉን አንገዛም። የምንገዛው ስለሰለቸን፣ ሌሎች ስላላቸው እኛም እንዲኖረን የመፎካከር ስሜት
ስለተሰማን፣ ወይም አርኪ ባልሆነ ህይወታችን ውስጥ ራሳችንን ለመካስ (ለመሸለም) ብለን ነው። ያ ለብቻችን ቁጭ ብለን የምናደርገው የኢንተርኔት
ግዢ፣ ያ ከከባድ ቀን በኋላ የምናደርገው የድንገተኛ ግዢ፣ ሁልጊዜ ራሴን ላዝናና የማለት ፍላጎታችን፤ ብዙ ጊዜ ስለ እቃው አይደለም። ባዶነት የሚሰማንን ቦታ ለመሙላት ነው እንጂ።
እዚህ ጋ ነው እንግዲህ ኢኪጋይ ሁሉንም ነገር የሚቀይረው። ህይወታችን አቅጣጫ ሲኖረው ምንነታችን ጠቃሚ
እንደሆንን ሲሰማን፣ ቀናችን ትርጉም እንዳለው አውቀን ስንነቃ፥ ያ ባዶነት መጥፋት ይጀምራል። ከህይወታችን ለመሸሽ አንፈልግም፤ ምክንያቱም ህይወታችን ራሱ መገኘት የምንፈልግበት ነገር ይሆናል። ትኩረታችን ከመግዛት ወደ መገንባት፣ ከመጠቀም ወደ መፍጠር፣ ጊዜያዊ ደስታን ከማሳደድ ወደ ዘላቂ እርካታ ይሸጋገራል። እናም አንድ ዝምተኛ ግን ጠንካራ ነገር ይከሰታል፤ የማውጣት ፍላጎታችን ይጠፋል—ይህ የሚሆነው ራስናችንን እንድንቆጥብ ስላስገደድን ሳይሆን፣ በቀላሉ ያን ያህል የመግዛት ፍላጎት ስለማይሰማን ነው። የበለጠ መራጭ፣ የበለጠ አስተዋይ እና ይበልጥ የተቃኘን እንሆናለን። ገንዘብ ከእንግዲህ ስሜታዊ ክፍተቶችን መሙያ አይሆንም፤ ትርጉም ላለው ህይወታችን ድጋፍ የሚሆን መሳሪያ ይሆናል። በዚያ ሽግግር ውስጥ ደግሞ አነስተኛ ወጪ አውጥተን የበለጠ እንኖራለን።
6. ሺንሪን-ዮኩ (Shinrin-Yoku)፦ ነጻ የተፈጥሮ ህክምናን እንደሰትበት 🌲 🧘♀️
በጩኸት፣ በማስታወቂያዎች እና ቀጣይነት ባለው መነቃቃት በተሞላች አለም ውስጥ፥ በጣም ቀላል በመሆኑ ብዙዎቻችን ጥንካሬውን ሙሉ በሙሉ የምንዘነጋው አንድ ልማድ አለ። "ሺንሪን-ዮኩ" ይባላል፤ ትርጉሙም "የጫካ ገላ መታጠቢያ" (Forest Bathing) ማለት ነው። ነገር ግን በስሙ እንዳንታለል፤ ምንም አይነት ውሃ የለበትም፣ ልዩ መሳሪያ አይፈልግም፣ ክህሎትም አይጠይቅም። ሺንሪን-ዮኩ በቀላሉ ይህ ነው፦ ወደ ተፈጥሮ መግባት እና በተፈጥሮ ውስጥ ሙሉ በሙሉ መገኘት ነው።
ስልክ የለም፣ ትኩረት የሚከፋፍል ነገር የለም፣ አጀንዳ የለም፤ እኛ እና የተፈጥሮ አለም ብቻ። ቀስ ብለን እንራመዳለን፣ የዛፎቹን አቀማመጥ፣ በነፋስ የሚንቀሳቀሱትን የቅጠሎች ድምጽ፣ የራሳችንን አተነፋፈስ እና የልብ ምት እናዳምጣለን፤
በመጨረሻም እንረጋጋለን።
ዛሬ በብዙ የዓለም ክፍሎች መዝናናት ወደ ንግድ ተቀይሯል። ዘና ለማለት ከፈለግን ገንዘብ ማውጣት እንዳለብን ይነገረናል፤ ስፓ (Spa) እንሂድ፣ የእረፍት ጊዜ እንያዝ፣ አዲስ ነገር እንግዛ እንላለን። ነገር ግን ሺንሪን-ዮኩ ፈጽሞ የተለየ ነገር ያቀርብልናል፤ በጣም ጠንካራ የሆኑት የፈውስ ዓይነቶች ነፃ መሆናቸውን ያስታውሰናል።
ሳይንስ ብዙ ባህሎች ሁልጊዜ የሚያውቁትን አስረግጦ ገልጿል፦ በተፈጥሮ ውስጥ ጊዜ ማሳለፍ የኮርቲሶል (Cortisol) መጠንን ይቀንሳል፣ ጭንቀትን ያስወግዳል፣ ስሜትን ያሻሽላል፣ አልፎ ተርፎም የበሽታ መከላከል ስርዓትን ያጠናክራል።
ነገር ግን ከሳይንሱ ባሻገር፣ ጥልቅ የሆነ የተፈጥሮ ስሜት አለ፤ ምክንያቱም የሰው ልጅ ሙሉ በሙሉ በኮንክሪት ግድግዳዎች እና በሚያበሩ ስክሪኖች ውስጥ እንዲኖር አልተፈጠረም። በውስጣችን የረጋ ክፍል አለ—የወፎችን ድምጽ፣ የዝናብ ጠረንን፣ የጫካውን ጸጥታ የሚያውቅ። እናም ከዛ ክፍል ጋር መልሰን ስንገናኝ፣ በውስጣችን ያለ ነገር ይረጋጋል። ደስታ ወጪ በማውጣት የምናሳድደው ነገር እንዳልሆነ እና በጸጥታ፣
በትንሽ ነገር፣ አሁን ውስጥ በመገኘት ልንለማመደው የምንችለው ነገር መሆኑን መረዳት እንጀምራለን። ያንን አንዴ ካወቅን በኋላ፣ በክፍያ በሚገኙ የመዝናኛ ዓይነቶች ላይ ያለን ጥገኝነት መላላት ይጀምራል። የማያቋርጥ መነቃቃት አያስፈልገንም። ልምዶችን ደጋግመን መግዛት አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ በሰላማዊ ቦታ ውስጥ በህይወት መኖር ብቻውን በቂ ነው።
7. ቴይኔ (Teinei)፦ በጥንቃቄ እና በማስተዋል እንኑር 🍵 🕯️
ነገሮችን ቀስ ብሎ በማድረግ ውስጥ የረጋ ውበት አለ፤ ከስንፍና ሳይሆን ከክብር የመነጨ በእርጋታ ውስጥ ይገኛል። ይህ የ"ቴይኔ" ምንነት ነው። ቴይኔ ማለት በጣም ትናንሽ በሆኑ ድርጊቶቻችን ውስጥ እንኳ በጥንቃቄ፣ በትኩረት እና በማስተዋል የመኖር ልማድ ነው። ብዙ ማድረግ ሳይሆን፣ ነገሮችን በተሻለ ሁኔታ ማድረግ ነው። በዛሬው አለም ሁሉም ነገር ፈጣን ነው፤ ፈጣን ምግብ (fast food)፣ ፈጣን ፋሽን (fast fashion)፣
ፈጣን ውሳኔዎች (Hasty decisions) የመሳሰሉ ነገሮችን እናስብ። ምግቦችን
ሳናስተውላቸው (ጣዕማቸውን ሳናውቅ) እንበላቸዋለን። ነገሮችን ሳናስብባቸው እንገዛቸዋለን። መጠገን የሚችል ትንሽ የመበላሸት ምልክት ስናይ ወዲያውኑ እንቀይረዋለን። እናም በዚያ ፍጥነት ውስጥ አንድ አስፈላጊ ነገር እናጣለን፦ እሱም ግንኙነት
(ቁርኝት) ይባላል።
ቴይኔ ፍጥነታችንን እንድንቀንስ እና መልሰን እንድንገናኝ ይጋብዘናል። ምግብናችንን በትኩረት እንድናብስል፣ ቦታችንን በጥንቃቄ እንድናጸዳ፣ ንብረቶቻችንን ዋጋ እንዳላቸው አድርገን እንድንይዛቸው—ያስተምረናል። ምክንያቱም ዋጋ አላቸውና። በዚህ መንገድ ስንኖር፣ ከፍጆታ (ከግዢ) ጋር ያለን ግንኙነት መለወጥ ይጀምራል። ምግብን አናበላሽም፣ ስለዚህ ብዙ አናባክንም። ንብረቶቻችንን ችላ አንልም፣
ስለዚህ ረዘም ላለ ጊዜ ያገለግሉናል። በችኮላ አንገዛም፣ ስለዚህ ፀፀትን
እናስወግዳለን። እያንዳንዱ ድርጊታችን ይበልጥ የታሰበበት ይሆናል። አስበን በማድረጋችን ያነሰ ብክነት፣ ያነሰ ጉዳት፣ ወጪ መቀነስ ይመጣል፣ አላማ
ከሌለው
ወጪ እንታደጋለን።
ነገር ግን እውነተኛው ለውጥ የገንዘብ ብቻ አይደለም፤ ስሜታዊም ጭምር ነው። ምክንያቱም የእለት ተእለት ህይወታችንን በጥንቃቄ ስንይዝ፣ በጣም ቀላል የሆኑት ጊዜያት እንኳ ትርጉም ይኖራቸዋል። ሰሃን ማጠብ መረጋጋትን ያመጣል። ምግብ ማዘጋጀት እርካታን ይሰጣል። ቦታችንን ማደራጀት መሰረት ይሰጠናል። ለትላልቅ እና ውድ ለሆኑ ጊዜያት መኖርን እናቆምና ትናንሾቹን እና ተራ የሆኑትን ማድነቅ እንጀምራለን። ይህንን ስናደርግ ደግሞ አንድ ጥልቅ ነገር እንረዳለን፦ ትርጉም ያለው ህይወት የማያቋርጥ ወጪን አይጠይቅም። ትርጉም ያለው ህይወት መገኘት (በትኩረት መኖር) መሆኑን እንገነዘባለን።
8. አነስተኛ (ሚኒማሊስት) የኑሮ ቦታዎች፦ አነስተኛ ቦታዎች፣ ትልቅ ቁጠባ 🏡 🪟
በብዙ የአለም ክፍሎች ስኬት ብዙ ጊዜ የሚለካው በስፋት ነው፤ ትላልቅ ቤቶች፣ ትላልቅ ክፍሎች፣ የሚሞሉ ብዙ ቦታዎች። ነገር ግን በጃፓን አካሄዱ የተለየ ነው። ቦታ ውስን ነው። ያንን እውነታ ከመታገል ይልቅ ይቀበሉታል። ቤቶች ሆነ ተብሎ አነስተኛ ተደርገው የተሰሩ ናቸው። ዲዛይኑ የታሰበበት ነው። እያንዳንዱ እቃ አላማ አለው። ይህ የህይወት ምርጫ ብቻ አይደለም፤ የአስተሳሰብ መንገድም ጭምር ነው። ምክንያቱም ቦታችን ውስን ሲሆን፣ ውሳኔዎችን ለማድረግ እንገደዳለን። እዚህ ለመኖር በትክክል የሚገባው ምንድን ነው? ለህይወቴ ዋጋ የሚጨምረው ምንድን ነው? ባዶ ቦታው የያዘው
ምንድን ነው ብለን እንድንጠይቅ ያረገናል።
እነዚህ ጥያቄዎች ሁሉንም ነገር ይቀይራሉ። በትንሽ ቦታ፣ በግዴታ ያነሰ ነገር እንገዛለን። አላስፈላጊ የቤት እቃዎችን እናስወግዳለን። ከመግዛታችን በፊት ሁለት ጊዜ እናስባለን። ከብዛት ይልቅ ለጥራት ቅድሚያ እንሰጣለን። በገንዘብ በኩል ጥቅሞቹ ግልጽ ናቸው፦ አነስተኛ ኪራይ፣ አነስተኛ የኤሌክትሪክ ክፍያ፣ አነስተኛ የጥገና ወጪ። ነገር ግን ጥልቁ ተፅእኖ ከገንዘብ በላይ ይሄዳል። ትንሽ ቦታ ለማስተዳደር ቀላል ነው፣ ለማጽዳት ቀላል ነው፣ ለመጠበቅ ቀላል ነው። በዚያም ምክንያት እጅግ ውድ የሆነ ነገር እናተርፋለን፦ ጊዜን። ትርፍ ነገሮችን በማጽዳት፣ በማደራጀት እና በመጠበቅ ልናጠፋው እንችል የነበረውን ጊዜ እናድናለን።
ከዚያ ጊዜ ጋር ደግሞ ነፃነት ይመጣል። የማረፍ ነፃነት፣ የማሰብ ነፃነት፣ በትክክል አስፈላጊ በሆነው ነገር ላይ የማተኮር ነፃነት። የስነ-ልቦና ለውጥም አለ፤ መዝረክረክ ጩኸትን ይፈጥራል። ብዙ ንብረቶች ትኩረትን ይቀንሳሉ። ነገር ግን ቀላል እና የታሰበበት ቦታ ግልጽነትን ይፈጥራል። አእምሯችን የስነ-ልቦና ነፃነትና ሰላም ያገኛል።አካባቢያችን
የተረጋጋ ይሆናል። ውጫዊው አካባቢያችን የውስጣዊ ማንነታችን እና
የህይወታችን ነጸብራቅ መሆን ይጀምራል። ያልተዝረከረክ፣ ውጥረት የሌለበት፣ ያለተጨናነቀ፤ የበለጠ ሰላም፣ የበለጠ ትኩረት፣ ይበልጥ ለቁጥጥር የሚያመች ቦታ እንፈጥራለን።
በመጨረሻም የሚያስፈልገን ብዙ ነገር ሳይሆን፣
የተሻለ ህይወት ምሆኑን አንድ ጠንካራ ነገር እንረዳለን።
መጀመሪያ ሲታይ እነዚህ የጃፓን መርሆች ቀላል ሊመስሉ ይችላሉ፤ ነገር ግን ጥንካሬያቸው የሚገኘው በቀጣይነት ላይ ነው። አነስተኛ ወጪ እያወጣን የተሻለ መኖር ማለት ከባድ መስዋዕትነት መክፈል ማለት አይደለም። እነዚህ መርሆች፦
በድንገት ከመግዛት ይልቅ ማስተዋልን፣ ከመቀየር ይልቅ ማድነቅን፣ ከግፊት ይልቅ አላማን መምረጥ የሚያስተምሩን ረቂቅ
ሽግግሮች (ለውጦች) ናቸው።
ሁልጊዜ ብዙ እንድንፈልግ በምትነግረን አለም ውስጥ፥ እነዚህ ፍልስፍናዎች ቀስ ብለው ያስታውሱናል—አሁንም ቢሆን በቂ አለን። እናም አንዳንድ ጊዜ በጣም ባለጸጋ የሆነው ህይወት፣ በጣም ቀላሉ ህይወት ነው። ይህ ፅሁፍ ስለ ገንዘብ
እና ስለ ህይወት ያለንን አስተሳሰብ ከቀየረው፣ ላይክ (Like) ማድረጋችንን፣ ሰብስክራይብ (Subscribe) ማድረጋችንን እና
ቀለል ያለ፣ ይበልጥ የታሰበበት የኑሮ ዘይቤ ለሚያስፈልገው ሰው ማጋራታችንን እናረጋግጥ። እናም ዛሬ ከእነዚህ የጃፓን መርሆች የትኛውን መተግበር እንደምንጀምር በኮሜንት (Comments) አጋሩን።
ምክንያቱም በተሻለ ሁኔታ የመኖር ጉዟችን የሚጀምረው በብዙ ገንዘብ አይደለም፤ በአዲስ አስተሳሰብ እንጂ።
"አነስተኛ ወጪ እያወጣን የተሻለ መኖር
ማለት ከባድ መስዋዕትነት መክፈል ማለት አይደለም።"


Comments
Post a Comment