ሁላችንም ቢሆን ቀላል እና ኪሳችንን ባማከለ መንገድ ቤታችንን ማስዋብና ማስተካከል እንፈልጋለን። ነገር ግን ከየት መጀመር እንዳለብን ፍንጭ ላይኖረን ይችላል። ቤትን ዲዛይን ማድረግ ከውጭ እንደሚታየው ቀላል አይደለም በተለይ በዲዛይን ስራ ላይ ምንም አይነት ዕውቀት እና ልምድ ለሌለው ሰው በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው። አንድን የዲዛይን ስራ ከመጀመራችን በፊት ብዙ ልናስባቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ። የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶችን አድርገን የነደፍነው ዲዛይንም መሬት ላይ ሲወርድ ብዙ ማስተካክያዎች እና ማሻሻያዎች ሊያስፈልጉት ይችላሉ። በዚህ ሙያ የሰለጠኑ እንደ ውስጣዊ ዲዛይነሮች(interior designers) እና አርክቴክቶች ግን አንድን ቦታ በተለያየ መንገድ እና ሁኔታ ለተፈለገው አገልግሎት እንዲውል አድርገው ዲዛይን ማድረግ የሚቻልበትን ቴክኒኮች ያውቃሉ ተምረውታልም።
ታድያ የውስጥ ዲዛይን እንዲሰሩልን የምንቀጥራቸውን ባለሙያዎች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። ምክንያቱም ቤታቸን የማንነታችን ማሳያ ከመሆኑ በተጨማሪ እነዚህ ባለሙያዎች እኛን ወክለው ብዙ የሚወስኑዋቸው ነገሮች አሉ። ለምሳሌ ጥሩ የሆነ ዲዛይነር ከእናንተ ጋር ብዙ ጊዜ በማሳለፍ የምትወዱትን እና የማትወዱትን ነገር ለማወቅ እንዲሁም ፍላጎታችሁን ለመረዳት ጥረት ያደርጋል። ይህን ማወቁም ለቤቱ ዲዛይን ትልቅ ግብዓት ነው ለቤቱ ዲዛይን የሚጠቀመው የስታይል አይነት፣ ቀለሞች እና ፈርኒቸሮች እንዲሁም ሌሎች የዲዛይን ስልቶችን ከእናንተ ማንነት ጋር የሚሄድ እንዲሆን ያደርገዋል። ነገር ግን ሙሉ በሙሉ የዲዛይነሩ ምርጫ እና ፍላጎት ብቻ ከሆነ ዲዛይኑ ለባለቤቱ ትርጉም የለሽ ይሆናል።
ዲዛይነሮች የተለያዩ የዲዛይን ዘይቤ ስሞችን ( design themes/styles ) እያነሱ ሲነግርዋችሁ ግር ሊላችሁ አይገባም። በእኛ ሀገር ከተለመዱት የዲዛይን ዘይቤዎች ውስጥ ዋናዎቹ contemporary , Modern eclectic, Classic, Mid-century Modern, Minimalist እና Scandinavian ይገኙበታል። ስለእያንዳንዳቸው ምንነት በቀጣይ ጊዜ የምናይ ይሆናል።

Comments
Post a Comment